ትምህርት ቤታችሁን እናስተዋውቃችሁ

ትምህርት ቤቱ ደረሰ ጣሰው አፀደ ህፃናት፣ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል። የትምህርት ቤቱ አመሰራረት እፁብ ድንቅ ነው። ...

የትምህርት ቤቱ አመሰራረት እፁብ ድንቅ ነው፡፡ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ተቋሙ ሊመሰረት የበቃው በሰሜን ጎንደር መስተዳድር ዞን በደባርቅ ከተማ አስተዳደር በምቃራ ቀበሌ ተወልዶ ያደገ አንድ ትልቅ ርዕይ ሰንቆ ሰፊ ውጣ ውረዶችን ተግቶ በማለፍ አትሌት በመሆን በጃፓን አገር የሚኖር ወጣት አለ፡፡ እሱም አትሌት ደረሰ ጣሰው ይባላል፡፡ ወላጅ ቤተሰቦቹም በዚሁ በምቃራ ቀበሌ ይገኛሉ፡፡ አትሌቱ በሩጫ ውድድር አቸንፎ ያገኛትን ገንዘብ እኔ ልጠቀምባት፣ ቤተሰቤ ይስተናገድባት አላለም፡፡ የትምህርት ቤቱ ፎቶ ወይም በሰፊ ከተማ በንግድ ስራ ተሰማርቸ ራሴን ልለውጥበት የሚል ግላዊ አስተሳሰብ አላደረበትም፡፡ እውነትም የህዝብ ልጅ ለህዝብ ተወልዶ በህዝብ መሃል አድጎ ለህዝብ የሚኖር ወጣት አትሌት በመሆኑ ለአደገበት አካባቢ በማሰብ በእውቀት፣በአመለካከት እና በክህሎት የታነፁ የቀየ ልጆቹን በብቃት ኮትኩቶ አሳድጎ መልካም ዜጋ ለማፍራት ቆርጦ ተነሳ ፤ሳይውል ሳያድር ያገኛትን ቋጥሮ ፕሮጀክት ቀርፆ ከጃፓን ወደ ምቃራ ከነፈ፣ ት/ቤት ለመክፈት ቦታ ጠየቀ፣ወላጆቼን ላግዝ ሳይል ትምህርት ቤት ለመክፈት የሃገሩን ህዝብ ይሁንታ እና የመስሪያ ቦታ አስፈቀደ 10000 ካ/ም መሬት በኢንቨስት መንት ተፈቀደለት፡፡ እናም በምቃራ ቀበሌ በሚገኘው ፀጥ ረጭ ባለው ሜዳ ላይ ለህፃናት ምቹ በሆነው አውላላ ሜዳ በ7000 ካ/ር ላይ መሬት በ2012 ዓ/ም የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠበት እና ሳይውል ሳያድር የግንባታ ስራውን አጧጧፈው፡፡ እናም ሃምሌ /2015 6 መማሪያ ክፍሎች፣3 ቢሮዎች፣3 መመገቢያ አዳራሾችን ሰርቶ አስመረቀ፡፡

በግንባታ ስራው ወቅት የተፈጠረ የስራ እድልን በተመለከተ

በጠቅላላ ከ3000 በላይ የአካበባቢው ማህበረሰብ ለ2 አመት በአናፂነት በረዳትነት እና በቀን ሰራተኝነት ጊዜአዊ የስራ እድል ተፈጥሮለታል፡፡ ይህ በገንዘብ ሲገመት 300000 ብር ይገመታል፡፡

ተማሪዎች

የትምህርት አጀማመር

በ2016 የትምህርት ዘመን በመዋእለ ህፃናት ከ1-3ኛ ክፍል ወንድ 133 ሴት 153 በድምሩ 286 ተማሪዎችን ወንድ 3 ሴት 12 መምህራን እና ወንድ 5 ሴት 8 በድምሩ 13 ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችን በመያዝ የመማር ማስተማር ስራውን አሃዱ ብሎ ጀመረ፡፡ ስራውን ለማስጀመር እና ቀጣይ ተግባራትን በዘመናዊ መንገድ እንዲፈፀሙ በማሰብ እና መማር ማስተማሩን ለማዘመን በማሰብ ኮምፒዩትር፣ፕሮጀክተር፣ሻሽ ቦርድ፣ ነጭ ሰሌዳ እና ሌሎች ዘመናዊ መማሪያ ቁሳቁሶን በማቅረብ እስካሁን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የትምህርት ቤቱ አደረጃጀት

በአንድ አርቆ አሳቢ እና ከግንባታ እስከ ማስተማር ድረስ ሰርቶ የማይደክም ስራ አሰኪያጅ፣ አንድ ከሙዚየም እስከ ባህላዊ ትውፊት ድረስ በማደራጀት የካበተ ልምድ ያለው ርእሰ መምህር እና አንድ በእንግሊዝኛ እውቀቱ ወደር የለለው፣ሰዎችን በማሰራት ግብረገብነቱ ወደር የለሽ ምክትል ርዕሰ መምህር እንዲሁም ህፃናትን በመንከባከብ እና እውቀት በማስጨበጥ ብቃታቸው በህዝቡ የተመሰከረላቸው መምህራን መዋቅሩን እያሰፋ ይገኛል፡፡

የትምህርት ቤቱ የማደግ ሁኔታ

በኬጅ 3 ያስቀጠላቸውን ተማሪዎች በመደበኛ 1ኛ ክፍል በማስቀጠል እና ትምህርት ቤቱ በህዝብ ተወዳጅነቱን እየጨመረ ስለመጣ ከሌላ ትምህርት ቤቶች የተቀበላቸውን ከ30 ላይ የ2ኛ ክፍል ተማሪዎች ይዞ ከፍተኛ ሞዴል ለመሆን በሩጫ ላይ ይገኛል፡፡ ተማሪዎች ከአሁኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገ እውቀት እንዲኖራቸው የኮምፒዩትር ትምህርት፣ አለምአቀፍ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ የንግግር እንግሊዝኛን ( spoken English) እንዲሁም በሃገር በቀል እውቀት እና በአስትሮኖሚ ምጡቅ እና ተመራማሪ እንዲሆኑ የግዕዝ ቋንቋን እንዲሁም ተማሪዎቻችን በስነ-ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ በማሰብ የግብረገብ ትምህርትን በስርዓተ ትምህርታችን በማካተት እያስተማርን እንገኛለን፡፡ የውስጥ እውቀታቸውን በማውጣት በመክሊታቸው እና ፍላጎታቸው አላማቸውን እንዲያሳኩ በአትሌት፣ በሙዚቃና ድራማ፣በባህላዊ እና ዘመናዊ ጨዋታዎች፣ በስነ-ፅሁፍ፣ በስእል እና ቅርፃቅርፅ እንዲሳተፉ በትጋት እየተሰራ ነው፡፡ ህፃናት ሃገራቸውን እና ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን በተግባር በተደገፈ ሁኔታ እንዲያውቁ እና የትምህርት ቤቱንም ሳቢነት ለማጉላት ትልቅ የሙዚየም ክፍል አዘጋጅተን የአካባቢውን ወግ ባህል እና ትውፊት የሚያሳዩ እቃዎችን በማደራጀት፣ታዋቂ የሃገር ባለታሪኮችን በፎቶ የተደገፈ መረጃ በማደራጀት ተማሪዎች እንዲያውቁት ከማድረጋችንም በላይ ሙዚየሙን በማህረሰቡ አስጎብኝተን በዞኑ ላሉ አንጋፋ ት/ቤቶችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑን ከተሰጠን አስተያየት ለመረዳት ችለናል፡፡ አሁንም ለማንኛውም አካል ለጉብኝት ክፍት ነው፡፡

የት/ቤቱ ባለቤት ለማህበረሰቡ እያበረከታቸው ያሉ ሌሎች ትሩፋቶች

አትሌቱ ህዝቡን አገልግሎ መርካት አልቻለም፡፡ ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ከመሀል ከተማ ጀምሮ የሰርቢስ አገልግሎት ፤ወርሃዊ ክፍያ ለሚቸግራቸው ወላጆች ህፃናቱ በነፃ እንዲማሩ በማመቻቸት የዋህ እና ለድሃ አዛኝ የህዝብ ልጅነቱን አስመስክሯል፡፡

የትምህርት ቤቱ ሳቢ እና ማራኪነት

ህፃናት ጨዋታ፣አዲስ ነገር ማየት የሚፈልጉ መሆኑን በመገንዘብ ዥዋዥዌ፣እሽክርክሪት፣ሚዛን፣መንሸራተቻ፣የመረብ ኳስ፣የቅርጫት ኳስ እና የእግር ኳስ ሜዳ ከነግብዓቱ በዘመናዊ መንገድ ተዘጋጅተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡በተለይ ደግሞ ህፃናቱ ከአሁኑ የውሳኔ ሰጭነት አቅማቸው እንዲያድግ የሚያደርጉ የውጭ የጌም፣የቪዲዮ ጨዋታዎች ትልቅ ትምህርታዊ መዝናኛዎቻችን ናቸው፡፡

ግቢው በቀጣይ

ተጨማሪ ክፍሎችን ስለሚከፍት ሁለት ብሎክ መማርያ ህንፃዎችን መገንባት ጀምሯል፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል የተፈቀደለት ቢሆንም አድማሱን በማስፋት እስከ 12ኛ ክፍል ለመቀጠል የከተማ አስተዳደሩ፣ ዞኑ፣ ቀበሌው፣ ኢንቨስትመንት አመራሩ ርይያችን እንዲፈፀም ማስፋፊያ ጠይቀን በመፍቀድ፣በሙያ እና አስተያየት በመደገፍ እና በማገዝ ለአበረታች ስራ አነሳስተውናል፡፡

ከዚህ ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎች ከአሁኑ መፃኢ እድል

አትሌት ደረሰ ትምህርት ቤቱን ሲከፍት ለትርፍ ሳይሆን ለሃገሪቱ መልካም ዜጋ ለማፍራት በመሆኑ ገና ከአሁኑ ከጃፓን ታዋቂ ግለሰቦች፣ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና ትምህርት ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር በትምህርታቸው ብልጫ ለሚያሳዩ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ጃፓን ሄደው የከፍተኛ ትምህርት እድል እንዲያገኙ ትምህርት ቤቱን በማስጎብኘት ቃል እንዲገቡ አድርጓል፡፡ መምህራን እና የትምህርት ቤቱ አመራሮች የጃፓንን መልካም አሰራሮች እና የህፃናት አያያዝ ልምድ አምጥተው እንዲጠቀሙ፣ የት/ቤቱን አሰራር ለማዘመን ተፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላትም የጎበኙት እንግዶች ቃል ገብተውልናል፡፡ ስለዚህ ት/ቤታችን የቀጣይ እድሉ ብሩህ ስለሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን እንጋብዛለን፡፡

የትምህርት ቤቱ ለትምህርት ምቹነት

ከድምፅ፣ከበካይ እና ሽታ ከሚፈጥሩ ሰው ሰራሽ ንክኪዎች ፍፁም ነፃ እና የራቀ መሆኑ ተማሪዎቻችን ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲማሩ በሚስጢራዊ ካሜራ የታገዘ 24 ሰኣት ጥበቃ የሚደረግ መሆኑ፤- ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተባብረን የምንሰራ በመሆኑ ህብረተሰቡ ራሱ አጥር ሆኖ እየጠበቀው መሆኑ ከምንም በላይ ት/ቤታችን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ውድ ደንበኞቻችን የእናንተ አስተያየት እና እገዛ ለነገ እድገታችን መሰረት ስለሆነ ከጎናችን አትለዩን እያልን የዛሬውን አበቃን የቸር ሰው ይበለን፡፡ በት/ቤቱ ማኔጅመንት የተዘጋጀ ሰኔ/2017ዓ /ም ኢትዮጵያ

↩️ ተመለስ